Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ በግል ት/ቤቶች ከሚያስተምሩ መምህራን 24 በመቶ የሚሆኑት በመምህርነት ሙያ ያልሰለጠኑ ናቸው- ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በግል ትምህርት ቤቶች ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል 24 በመቶ የሚሆኑት በመምህርነት ሙያ ያልሰለጠኑ መሆናቸውን የአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና፣ ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
 
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋጋር የማስተማር ስነ-ዘዴ ስልጠና ያልወሰዱ መምህራንን የማሰልጠን ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
 
በአዲስ አበባ ከመንግስት ትምህርት ቤት ወጪ 1 ሺህ 562 ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን÷ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥም ከ23 ሺህ 400 በላይ መምህራን እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
 
በባለስልጣኑ የመምህራንና የትምህርት ቤቶች አመራር ፈቃድ ቡድን መሪ አቶ ሰንደቁ ያዛቸው እንደተናገሩት÷በመዲናዋ በመምህርነት ሙያ ያልሰለጠኑ እና ባልሰለጠኑበት የትምህርት ዓይነት የሚያስተምሩ በርካታ መምህራን አሉ።
 
በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ችግሩ በስፋት እንደሚታይም ነው ቡድን መሪው ያነሱት፡፡
 
በ2013 ዓ.ም የተደረገው ጥናት በከተማዋ በግል ትምህርት ቤቶች ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል 24 በመቶ የሚሆኑት በመምህርነት ሙያ ያልሰለጠኑ መሆናቸውን አመልክቷል።
 
በመንግስት ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ ከሚገኙት መካከልም አራት ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆኑ መምህራን ባልሰለጠኑበት የመምህርነት ሙያ በማስተማር ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
ይህም ለትምህርት ጥራት መጓደል የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ገልጸው÷ ችግሩን ለመቅረፍ የከተማዋ ትምህርት ቢሮና ትምህርት ሚኒስቴር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
 
በባለስልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና የሚወስዱ ማናቸውም መምህራን በመጀመሪያ የመምህርነት ሙያ ስልጠና ሊወስዱ እንደሚገባ የሚያስገድድ መመሪያ በመኖሩ ምክንያት በርካታ መምህራን በግላቸው ስልጠናውን እየወሰዱ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው÷በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የማስተማር ስነ-ዘዴን ያልወሰዱ መምህራን መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ይህም ለትምህርት ጥራት መጓደል የሚያስከትለውን ተጽእኖ በመገንዘብ ለመምህራኑ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው÷ለአብነትም በቅድመ መደበኛ ለሚያስተምሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ መምህራን ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
 
አቶ ሳምሶን ለመምህራን የሚሰጠው ስልጠና በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ችግሮቹን ለመፍታት ቢሮው ከኮተቤ ሜትሮፓሊታን እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከደብረብርሃን መምህራን ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version