Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የታሸገን ንግድ ቤት አስከፍታለሁ በማለት 100 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የስራ ኃላፊ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ ፈቃድ ለማሳደስና የታሸገ ንግድ ቤት አስከፍታለሁ በማለት 100 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የስራ ኃላፊ እጅ ከፍንጅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ የንግድ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ታሽጎ የነበረውን አቤኔዘር የተሽከርካሪ እጥበት አገልግሎት ድርጅትን ለማስከፈት እና የንግድ ፈቃዱ እንዲታደስ አደርጋለሁ በማለት 100 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።
የድርጅቱ ባለ ንብረት በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ታሽጎ የነበረው ድርጅታቸው እንዲከፈትና ንግድ ፈቃድ እንዲታደስላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የስራ ኃላፊው 100 ሺህ ብር ጉቦ እንዲሰጠው መጠየቁን የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መረጃ ይደርሰዋል፡፡
መምሪያው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ግለሰቡ 22 ጎላጎል ህንጻ በሚገኘው ካፌ ውስጥ ብሩን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል።
በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰል ያተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሹ የስራ ኃላፊዎችም ይሁኑ ባለሙያዎች ሲያጋጥሙ ህብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የመስጠት ልምዱን እንዲያጠናክር ፖሊስ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ጠይቋል።
Exit mobile version