አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎችና ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ስራ መግባቱን የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ ÷ ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫና ውሳኔ መሰረት ከህዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከሕዝብ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የአጭርና ረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ በክልል ደረጃ በእቅዱ መሰረት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙና በየአራት ቀናት ከአመራሩ ጋር እየገመገመ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የክልሉን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችለውን የ90 ቀን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ገልጸዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ከተደረጉ በኋላ ከመጋቢት 29 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑንም አመላክተዋል።
በትግበራው ምዕራፍ በፓርቲው የተቀመጡ ግቦችን መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት በሚመለከተው ልክ የራሱን መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምጦ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ወራትም በክልሉ መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ሌብነትን የሚጠየፍ ማሕበረሰብ የመፍጠር ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል ማለታቸውን ከሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

