Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ለተፈናቀሉ ዜጎች 43 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ለተፈናቀሉ ወገኖች 43 ሚሊየን ብር የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጋለች።
 
የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተፈራ ታሎሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ድጋፉ በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን በጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ነው፡፡
 
የተደረገው ድጋፍ አልሚ ምግብ፣ ዘይት፣ ባቄላ እና ዱቄት ያካተተ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ÷ 15 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
 
በኩታበር ወረዳ ቻይና ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን የተደረገላቸው የዕለት እርዳታ ድጋፍ ከጊዜያዊ ችግራቸው እንደሚያላቅቃቸው ገልፀው÷በቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
 
በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ስም የተደረገውን የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ ቲር እና ሲ ኤፍ ጅ ቢ የተሠኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
 
በደቡብ ወሎ ዞን በሚደረገው ድጋፍ ቃሉ፣ አርጎባ ፣ መቅደላ እና ቦረና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
 
በእሸቱ ወ/ሚካኤል
Exit mobile version