አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምርጫ ወቅት በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ፖለቲካዊ ቀውስ እና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ መሰራት እንዳለበት ምሁራን ገለጹ፡፡
ምሁራኑ ምርጫ በመጣ ቁጥር በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ተጽኗቸው ከባድ መሆኑን አፍሪካውያን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ለዚህም የወጡ ህጎችን ተግባር ላይ ማዋል እና ሀሰተኛ መረጃዎችን እያጣሩ ለዜጎች በፍጥነት ማቅረብ ጊዜው የሚጠይቀው ሃላፊነት መሆኑን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡
የሴኔጋል፣ አልጀሪያ፣ ቻድ እና ጣልያን የሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ተመራማሪዎች፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ ምርጫዎች በማህበራዊ ትስስር ሚዱያ የተለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥረው ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ የያዘችው ኢትዮጵያም በእነዚህ ሀገራት የተከሰቱ ችግሮች እንዳይደገሙ ልምድ መውሰድ ይገባታል ነው ያሉት።
ሴኔጋላዊው የሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ተመራማሪ ኤሪክ ፉዋዴ፥ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ጥረት መቀልበስ እንደሚቻል አንስተዋል።
አልጀሪያዊው ወጣት ተመራማሪ ሃምዳን ቡርጃ በበኩሉ፥ ሀሰተኛ መረጃ በሁሉም አካባቢዎች እየተሰራጨ መሆኑን አንስቶ አጠራጣሪ መረጃዎችን ስናገኝ ለእውነት ፍለጋ መድከም አለብን ብሏል፡፡
መንግስታት ህግን ከማውጣት ባለፈም ተግባራዊ ማድረግና ለአፈፃፀማቸው መትጋትም ሌላኛው የሀሰተኛ መረጃ መቀልበሻ መንገድ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
አያይዞም በምርጫ የሚሳተፉ ፖለቲከኞች ከሀሰተኛ መረጃ በመራቅ ርዕዮተ ዓለም እና ፖሊሲ ስትራቴጂ ማጥናት ላይ ትኩረታቸውን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል፡፡
በምርጫ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ሀሰተኛ መልዕክቶችን መከላከል የምንችለው ፊት ለፊት ውይይት ሲካሄድ መሆኑን ጣሊያናዊው የሰላም ጉዳዮች ባለሙያ ፔናኒዞ ይናገራሉ፡፡
ለዚህም ማሳያ የጁባ ሹማምንት እና ተፋላሚ ሃይላት ላለፉት ዓመታት የተቃርኖ ምንጫቸው ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዜናዎች ነበሩ ብለዋል።
ቻዳዊው ክሌማ አቦፌታም፥ ሀሰተኛ መረጃዎች የበርካታ ሰዎችን አዕምሮ እየገዙ መሆኑን ጠቅሰው፥ ወጣቶች በሀሰተኛ መረጃ ከመጠመድ እና ለዚያ ግብረ መልስ ለመስጠት ከመጣደፍ መውጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከጎሳዊ ውግንና ተሻግረው ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ዓለም አቀፍ ዕሳቤዎችን ለሚያራምዱ መረጃዎች ጆሮ መስጠት አለባቸው ሲሉም መክረዋል፡፡
በስላባት ማናዬ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision