አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጃፓን ፉኮካ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ከሆኑት ማጹፉጂ ኮጂ ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ከተሞች ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ መክረዋል።
የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገ ያለውን ድጋፍ ያደነቁት አቶ ገዱ፥ ፉኮካ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ከተሞች ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል።
ፕሮፌሰር ማጹፉጂ ኮጂ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የጃፓን ከተሞች ከአካባቢው የአየር ንብረት እና የመሬት አቀማመጥ ጋር የተጣጣመ በአነስተኛ ወጪ ዘላቂ የሆነ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ውጤታማ ስራ እያከነወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፅህፈት ቤት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
እንዲሁም በኬንያ ከሚገኘው የጆሞ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ እና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በመስራት ቴክኖሎጂውን ለናይል ተፋሰስ ሃገራት በስፋት የማስተዋወቅ እቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ነው፤

