አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፕሮጀክቶች መጓተት እንደ ችግር በሚነሳው ጊዜያዊ የፍርድ ቤት እግድ ላይ የሚመክር መድረክ በአዲ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የአዲ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፍትሕ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ዐቃቤያነ ሕጎችና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚከራከርባቸው መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች እና የፍርድ ቤት ጊዜያዊ እግዶች” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጠና ጥናት ቀርቧል፡፡
ጥናቱ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የመፍትሔ አማራጮችና የትግበራ መመሪያዎችን ማካተቱ ተጠቁሟል።
በውይይቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት÷ ከተማችንን በጋራ ለማልማት እና ችግሮችን በጋራ ትብብር ለመፍታት ጥናት ላይ መሰረት አድርጎ መሥራት ይገባል፡፡
የሀገር ልማት እንዲፋጠን በውይይቱ የሚነሱ ምክረሃሳቦችን ለመተግበር እና በአፈፃፀም በኩል እንደችግር የሚነሳ ቢኖር ለማስተካከል ቁርጠኛ መሆናቸውንም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
የአዲ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፅዋዬ ሙሉነህ የከተማዋን ሁለንተናዊ ልማት ለማከናወን መጓተት ከሚፈጥሩት ችግሮች መካከል አንዱ የፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ እግዶች መሆናቸውን ጠቁመው÷ ለውይይት የቀረበው ጥናትም የተቀላጠፈ፣ ፍትሐዊ እና የመንግስት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለይቶ ለውይይት ያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀብታሙ ተ/ስላሴ

