Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህዳሴ ግድብ የሃገር ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልድና የሃገር ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
 
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በግድቡ የድርድር ሂደት፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤት በሰጠው መግለጫ እና ቀጣይ መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በግብፅ በሚነሱ የስጋት ሀሳቦች ዙሪያ አሜሪካና የአለም ባንክ በታዛቢነት በተገኙበት ድርድር ቢጀመርም አሜሪካ ከታዛቢነት ወደ ተደራዳሪነት ተቀይራ በግምጃ ቤቷ በኩል በግድቡ ውሃ አሞላል የተመለከተ መግለጫ እስከማውጣት ደርሳለች።
 
አሜሪካ ከዚህ በተጨማሪ ለስምምነት ፊርማ የሚያርፍበት ሰነድ እስከማዘጋጀት መጓዟ የኢትዮጵያን ጥቅም እና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ድርጊት ሆኗል።
 
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና፥እስራኤል፣ ግብጽና አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የሚያስተሳስራቸው በርካታ የጋራ ጥቅም እንዳላቸው ያነሳሉ።
 
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ወደ ድርድር ጠረጴዛው መግባት አልነበረባትም የሚሉት ፕሮፈሰሩ፥ይሁን እንጂ በድርድሩ እውቀትና የሃገር ፍቅር ያላቸው ዜጎችን በመመደብ የተደረገው ጥረት መልካም መሆኑን ጠቁመዋል።
 
የግድቡን ግንባታ በጋራ ከዳር ለማድረስ ከመተባበር ባለፈ በግብፅ ዙሪያ የተሰበሰቡ ሃገራትን ሁኔታ ማጤን አፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
 
የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፥ አሜሪካኖች ለራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም የሚሰሩ በመሆናቸው ከጅምሩ በህዳሴው ግድብ ላይ ታዛቢ ለመሆን የሚያስችል ምክንያት እንደሌለ አብራርተዋል።
 
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት በሂደቱ የሃገር ጥቅም የሚጋፉ ነገሮች መኖራቸውን ተገንዝቦ የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
 
የድርድሩ ሂደት ተቋርጦ ጉዳዩ ወደ ሚመለከታቸው የአፍሪካ ሃገራት መመለስ አለበት የሚሉት አቶ ልደቱ፥ለዚህም 10 የተፋሰሱ ሃገራት መኖራቸው በቂ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።
 
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር አለም አቀፉ ማህበረሰቡ በቀላሉ የሚመለከተው ጉዳይ ባለመሆኑ መንግስት ድርድሩን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣቱ ተገቢነት ያለውና አዋጭ መሆኑንም አውስተዋል።
 
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ ብርሄ፥በየትኛውም ቦታ የሃገርና የህዝብን ጥቅም እና ሉዓላዊነት በድርድር ማስጠበቅ ይገባል፤ከድርድር ሂደቱ ባለፈ በቀጣይ በህዝብና በመንግስት ምን መደረግ አለበት ለሚለው ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።
 
አቶ ልደቱ አያሌው ሃገራዊ ህልውናችን እና ሉዓላዊነታችን ማሳየት የምንችለው በየትኛውም ሃይል ሳንደናቀፍ የግድቡን ግንባታ ዳር ማድረስ ስንችል ነው ይላሉ።
 
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልድና የሃገር ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁሉም የሚረባረብበት ጊዜው አሁን መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህም ግድቡ ሲጀመር እንድነበረው ሁሉ ያለምንም ልዩነት ርብርብ በማድረግ ግንባታውን ማጠናቀቅ የጋራ የውዴታ ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
ዶክተር አረጋዊ ህዝብ ከሚያደርገው ርብርብ ባሻገር በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩልም ለሃገርና ህዝብ ጥቅም እንዲሁም ሉዓላዊነት መከበር በጋራ መቆም አስፍላጊ መሆኑን ተናግረዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተፈራረሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ይሄን የሚያዝ መሆኑን በመጥቀስ።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የጋራ ታሪካችን የሚሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ ለማድረስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
 
በበላይ ተስፋዬ
Exit mobile version