አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሕግ ማስከበር ዘመቻው መስዋዕትነት ለከፈሉና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የጸጥታ አካላት የማዕረግ ዕድገት፣ ዕውቅናና ሽልማት ሰጠ፡፡
የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ ፖሊስና ጸረ ሽምቅ አመራሮችና አባላት፣ ጉዳት ለደረሰባቸው የጸጥታ አካላት፣ በግዳጅ ለተሰው አባላት ቤተሰቦች እንዲሁም በሕግ ማስከበር ሥራው ላይ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትም ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ለክልሉ የጸጥታ አካላት የተሰጠው ዕውቅናና ሽልማት የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ላደረጉትተጋድሎና ለከፈሉት መስዋዕትነት ክብር ከመስጠት ባሻገር ለቀሪ ስራቸው የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ የክልሉ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው÷ ለሕገ መንግስቱና ለሕዝቡ ታማኝ የጸጥታ አካላት የከፈሉት መስዋዕትነት ሁልጊዜም ክብር እንደሚሰጠው አመላክተዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀሩን ዑመር በበኩላቸው÷ ተላላኪ ኃይሎች ክልሉን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት የጥፋት ተልዕኮውን ለመቀልበስ የክልሉ የጸጥታ አካላት ከፌዴራልና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሕይወታቸውን ከፍለዋ ብለዋል፡፡
የተጀመረው የምስጋናና ዕውቅና መርሐ ግብር መስዋዕትነት የከፈሉ የጸጥታ አካላትን ክብር ከመስጠት ባለፈ የተቋሙ ሪፎርም አንዱ አካል በመሆኑ÷ በሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች ይቀጥላል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

