አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመላው ህዝባችን የሰላም እና ደህንነት ጋሻ ለመሆን የሚያስችለንን አቅም እየገነባን ነው ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ተናገሩ፡፡
የፖሊስ አመራርና አባላት የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጠላቶቻችን ከፍተውብን የነበረውን ጥቃት ለመመከት የፖሊስ ሰራዊት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት አኩሪ ገድልና ጀግንነት ፈፅሟል ብለዋል፡፡
የወንጀል መከላከል አቅማችንም እየጎለበተ መጥቷል ያሉት ኮሚሽነር ደመላሽ ለመላው ህዝባችን የሰላም እና ደህንነት ጋሻ ለመሆን የሚያስችለንን አቅም እየገነባን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዛሬው መርሃ ግብርም ተቋማዊ የአቋም ግንባታንና የላቀ የስራ አፈፀፃፀም ወደ ተሸለ ደረጃ ለማሸጋገር ተልኮ ፈፃሚውና በየደረጃው ያለውን አመራርና አባል ለበለጠ ሃላፊነት የሚያነሰሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በህግ ማስከበር ፣ በህልውና እና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻዎች ወቅት ጀግንነት የፈፀሙና የላቀ የስራ ውጤት ያስመዘገቡ በየደረጃው ያሉ የፖሊስ አመራርና አባላት፣ ከፍተኛ መኮንኖች እና ሌሎች ለዕውቅናና ለምስጋና መርሃ ግብሩ መመረጣቸውን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ምርጥ ሙያተኞች የልዩ የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ይሆናሉ ያሉ ሲሆን፥ እንዲሁም በግዳጅ ላይ በክብር የተሰዉ ጓዶችን እና ቤተሰቦቻቸውን የምናመሰግንነበት ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም የፍትህ አካላት እና መንግስት ላደረገልን ድጋፍ እና ክትትል ዕውቅና የምንሰጥበት ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ መርሃ ግብሩ በቀጣይም በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ ጠቅላይ መምሪያዎች እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው

