Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ጎንደር ዞን በህግ ማስከበር ስራው ከ775 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በደቡብ ጎንደር ዞን በተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ከ775 በላይ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገልፀዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንደገለፁት በደቡብ ጎንደር ዞን ከህልውና ዘመቻው ማግስት የወንጀለኞች መበራከት፣ የግድያ፣ ተደራጅቶ መዝረፍ፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና የመሳሰሉት ህገ ወጥ ድርጊቶች አስከፊ እየሆኑ መጥተዋል።

በርካታ የዞኑን ገፅታ የሚያበላሹና ሰው በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የሚያደርጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ህግ እንዲከበር ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በመስራት እና ከህዝቡ ጋር መግባባት በመፍጠር በርካታ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጀመረው የህግ ማስከበር ስራም 775 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለህግ የቀረቡ ሲሆን የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዞኑ የህግ ማስከበር ስራው ከተጀመረ ወዲህ የሰው ሞት፣ የጥይት ተኩስና ሌሎች ወንጀሎች በእጅጉ መሻሻላቸውንና ህዝቡ የእፎይታ ጊዜ ማግኘቱን አብራርተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ በደስታም ሆነ በመከራ ሲተኩስ የተያዘ ሰው ሙሉ ትጥቁ ለመንግስት ገቢ እንሚሆን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡን እያማረረ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት በተመለከተም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ቁጥጥር እንዲደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደቡብ ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን ያኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version