አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ሶስተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለፀ፡፡
በአስተዳደሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሽታን ለመከላከል እስካሁን በተከናወኑ ሁሉን አቀፍ የመከላከል ተግባራት ባለፉት ሁለት ዙሮች በተሰጠው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት አማካኝነት የወረርሽኙ ስርጭት መጠንና በቫይረሱ ለከፍተኛ ህመምና ሞት የሚዳረጉ ህሙማን ቁጥርን መቀነስ መቻሉ ተገልጿል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሁለት ዙሮች በተሰጠው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትም ከ180 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ክትባቱን መውሰዳቸው ታውቋል፡፡
በቀጣይም ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው ሶስተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከ95 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ለመከተብ እንደታቀደ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
በዚህም ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞቻቸውን የማስከተብ ሀላፊነት ያለባቸው በመሆኑና በሁሉም የከተማና የገጠር ቀበሌዎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ክትባቱ የሚሰጥ በመሆኑ እድሜያቸው ከ12 አመት በላይ የሆኑ ነዋሪዎች በሙሉ ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ክትባት ዘመቻ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መጠየቃቸውን ከከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

