አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሐረር ፖሊስ ሆስፒታልን ለማስፋፋት የውል ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የገባው ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር ሲሆን፥ ስምምነቱን የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል እና የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሰለሞን ደመቀ ተፈራርመዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል እንደገለጹት፥ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የሚገነባው በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ፣ የሀረሪ ፖሊስ፣ የሶማሌ ፖሊስ እና የሰራዊቱ ቤተሰቦች እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ የህክምና አገልግሎቱን በቅርበት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ነው።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሰለሞን ደመቀ በበኩላቸው፥ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በፍጥነትና በጥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ለማስረከብ እንሰራለን ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

