አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባትን ለዜጎች ለማዳረስና የጤና ዘርፉን ለማገዝ የ195 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባቶችን በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍና በግጭቶች የተጎዱ የሕዝብ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ነው ተብሏል።
ወቅታዊው የገንዘብ ድጋፍ በጫና ውስጥ ላለው የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት አጋዥ ከመሆን በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በታች ያለውን የኮቪድ-19 የክትባት ሽፋን ለማሳደግና በመላ አገሪቱ የክትባት ሥራዎችን በማስፋፋት የበሽታውን ስርጭትና ተጽዕኖ ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተናግረዋል።
በእናቶች እና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ረገድ ፣በሥነ-ምግብ እና ሌሎች ቁልፍ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያም የገንዘብ ድጋፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና በግጭቱ የተጎዱ የገጠር አካባቢዎችን እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ብሎም ለኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ታወቋል፡፡
በተጨማሪም ድጋፋ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ግዢ ለማድረግ ፣የሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ክፍል መሳሪያዎችን ለማሟላት ፣ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ህመሞች ላይ ያሉ ህመምተኞችን አያያዝ የበለጠ ለማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ይውላል መባሉን ከፋይናንስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡
የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 መጨረሻ ለ60 በመቶ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን÷ይህ የ195 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ምላሽ የሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ከ495 ሚሊየን ዶላር ያደረሰው መሆኑ ታወቋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

