አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል በማፍራትና ምርምር ከማከናወን ባለፈ የዲፕሎማሲ ኃይል መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለፁ።
“የዩኒቨርሲቲ እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ ጠንካራ አመራር”በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ “የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ችግር ፈቺና የኢንዱስትሪ ምርታማነትን የሚያሳድግ እንዲሁም ግብርናን የሚያዘምን ምርምር ከማከናወን ባሻገር የዲፕሎማሲ ኃይል መሆን ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲ እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረሙ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሳተፉባቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያ የምትከተለውን የብሔራዊ ጥቅም አተያይ ለማስገንዘብ መስራት እንደሚኖርባቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብሄራዊ ጥቅምን መነሻ የሚያደርግ በትብብርና በፉክክር ሚዛን አስጠብቆ የሚከናወን እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተጨማሪ “ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በላቀ ደረጃ የሚረጋገጥበትን ሥልት በጥናት ለይቶ ከማመላከት አልፈው በሚሳተፉባቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ የብሔራዊ ጥቅም አተያይን ማስገንዘብ ይኖርባቸዋልም” ነው ያሉት።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም በድርድር በሚመጣ መፍትሔ ውስጥ የሃገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ውጤት እንዲገኝ የትምህርት ተቋማት ብዙ መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በዛሬው እለት የተጀመረው የምክክር መድረክ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

