Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሊያከብር ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ አጠራሩ ፖሊ-ቴክኒክ ኢንስቲቲዩትይሰኝ የነበረው የአሁኑ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሊያከብር ነው።
የምስረታ በዓሉ የፊታችን መስከረም ወር ሙሉ 50 ዓመት በሚሞላው የቀድሞው የፔዳጎጂ አካዳሚ የምስረታ በዓል አከባበር ተጀምሮ ለዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ምስረታ መነሻ የነበረው የቀድሞው ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲቲዩት 60ኛ ዓመት የሚሞላበት ሰኔ 04 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ተናግረዋል፡፡
የበዓሉን መከበር አላማ አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ዶክተር ፍሬው÷ ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጣቸውን ራዕይ፣ ተልዕኮዎችና ግቦች ለማሳካት ተጨማሪ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ዩኒቨርሲቲው በተጓዘባቸው ዓመታት ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች የተቋሙ ብሎም የውጪው ማህበረሰብ ይበልጥ እንዲያውቃቸውና ለቀጣዩ የዩኒቨርስቲው ራዕይ መሳካት በቅንጅት እንዲነሳሳ ለማገዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለዩኒቨርሲቲው የዛሬ ቁመና በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ የነበራቸውን አካላትና በምርምር፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች እውቅና ያገኙ አካላትን ለማመስገን ብሎም ለወደፊቱ በጋራ ለመምከርተቋሙን አገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ክሱትነትና ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው÷ የዩኒቨርሲቲው የምስረታ በዓል የከተማዋም በዓል በመሆኑ በርካታ ተግባራትን በቅንጅት እንደሚሰሩ ሁሉ ይህንን በዓልም በጋራ እንደሚያከብሩት ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳደሩና ነዋሪው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማጠናከርም ልዩ ልዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የ60ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በልዩ ልዩ ሁነቶች የሚከበር መሆኑንም ዶክተር ፍሬው በማብራሪያቸው ጠቁመዋል፡፡
በሙሉጌታ ደሴ
Exit mobile version