Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በካፋ ዞን በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን የቡና ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ÷ቡና የክልሉ ልዩ እሴት መሆኑን ጠቅሰው የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የክልሉን አርሶአደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት ይሰራል ብለዋል።

በዞኑ የቡናን ምርታማነት ለማሳለጥም የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።

ቡና ለአካባቢው ማህበረሰብ ከኢኮኖሚ አልፎ የማህበራዊ መስተጋብር መገለጫ ነው ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ይህንን ልዩ እሴት በአግባቡ ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ቡናን ማልማት የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ጠብቆ ለማቆየት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፥ አሁን ያለው የዓለም ግብይት ስርዓት አመቺ በመሆኑ አምራች አርሶ አደሮች በደላሎች ሳይበዘበዙ በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ ለቡና ማስፋፊያ ከ76 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ እንደሚተከል መግለፃቸውን ከዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version