አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 192 ሺህ ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ተወካይ ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በመንግስት፣ በግለሰብ፣ በተቋማት፣ በማህበራትና በወጣቶች የተፈላ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ በችግኝ ተከላው ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን፥ እስካሁን ከ270 ሚሊየን በላይ የችግኝ ጉድጓድ ዝግጅት ተደርጓል።
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአንድ ጀምበር ከ250 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከልም ነው የተገለጸው።
መርሐ ግብሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ክትትልና ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በማህበራት የተደራጁ ከ11 ሺህ በላይ ወጣቶች የደን፣ የፍራፍሬና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በማፍላት በሽያጭ ለተከላ ማዘጋጀታቸውንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ አቶ መልካሙ ጌቴ በበኩላቸው ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷልም ብለዋል።

