አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የበለጸጉ ሀገራት በከባቢ አየር ላይ በሚያደርሱት ብክለት ለደረሰው ጉዳት ለታዳጊ ሀገራት ካሳ እንዲከፍሉ ተጠየቀ፡፡
ታዳጊ ሀገራት የማካካሻ ካሳውን የጠየቁት በጀርመን ቦን እየተካሄደ ባለው የዓየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚመክር ስብሰባ ላይ ነው፡፡
ታዳጊ ሀገራቱ ምንም እንኳን ከፍተኛው የከባቢ ብክለት እና የጎጂ ኬሚካሎች ልቀት የሚወጣው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ሀገራት ቢሆንም እነዚህ የበለጸጉ ሀገራት ግን ጉዳዩን ወደ ጎን ገፍተውታል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ዘጋቢ የሆነው ማት ግራት እንደሚለው ÷ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የታዳጊ ሀገራት ተወካዮች “በዓየር ንብረት ላይ የሚደርሰው ብክለት ከበለጸጉት ሀገራት ይልቅ የከፋ ጉዳት የሚያደርሰው በእኛ ላይ ነው፤ ጉዳቱን የመቋቋም አቅማችንም አነስተኛ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ለደረሰው ጉዳት እና ውድመትም የበለጸጉት ሀገራት ካሳ እንዲከፍሉ ጠይቀዋል፡፡
የበለጸጉት ሀገራት በየጊዜው የሚያደርሱትን የከባቢ አየር ብክለት ለመቀነስ በፓሪስ ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
ከዚህ ባለፈም የበለጸጉ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ጋዝ ለመቀነስና ታዳጊ ሀገራት ለሚደርስባቸው ጉዳትና ጫና ገንዘብ መክፈልን ያካትታል።
ይሁን እንጅ ሀገራቱ በስምምነቱ መሰረት ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አይደሉም፤ የገቡትን ቃልም አጥፈዋል በሚል የታዳጊ ሀገራት ተወካዮች ኮንነዋል።
የበለጸጉ ሀገራት “የገባነውን ቃል ብንፈጽም በቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ያሳጣናል” በሚል ጉዳዩን ከመቀበል ይልቅ ሲገፉት ተስተውለዋልም ነው የተባለው፡፡
ቢሆንም ግን ሊጠናቀቅ አንድ ቀን በቀረው ስብሰባ ላይ የበለጸጉት ሀገራት ላደረሱት ጉዳት ለታዳጊ ሀገራቱ ካሳ ሊከፍሉ የሚችሉበት ዕድል እንዳልተሟጠጠ እና ተሥፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንደተስተዋሉ ማት ግራት ገልጿል፡፡

