Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለበልግና መኸር እርሻ 15 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ይሰራጫል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጭው የበልግና መኸር እርሻ ስራ 15 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ሊሰራጭ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የግብአት አቅርቦት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ይህን እውን ለማድረግም የግብርና ሚኒስቴር በየአመቱ በተለይም በመኸር ወቅት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የግብርና ግብአቶችን ያቀርባል።

በዚህ አመትም የግብርና ግብአት ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እና በጊዜው ቀድሞ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

አቶ ሳኒ እንዳሉት ለበልግ እና ቀጣይ መኸር ወቅት 15 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ይሰራጫል።

ከሚሰራጨው ማዳበሪያ ውስጥ 14 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታሉ ከውጭ የሚገባ ሲሆን፥ 500 ሺህ ኩንታሉ ደግሞ ካለፈው የምርት ዘመን የተረፈ ማዳበሪያ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥም 30 በመቶ ያህሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ጠቅሰው፥ ለማዳበሪያ ግዥ 29 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መመደቡንም ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታሉ ሀገር ውስጥ በተዘጋጁ የማከማቻ ወይም ማዕከላዊ መጋዘን ሲገባ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታሉ ደግሞ ወደብ ደርሷል።

በአጠቃላይ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ማዳበሪያው ተጠናቆ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ማዳበሪያውን የዘር ወቅት ከሚጀመርበት 1 ወር በፊት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን ምርጥ ዘር ላይ የሚስፈልገውን ያህል ለማሰራጨት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የምርጥ ዘሩን ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሳኒ ስራው የሚሰራባቸው ላቦራቶሪዎች ምርጥ ዘሩን የመለየት እና የማጣራት ስራ መጀመራቸውንም አውስተዋል።

በዙፋን ካሳሁን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version