አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊልም ኢንዱስትሪን በምሥራቅ አፍሪካ በማስፋፋት በርካታ የሥራ ዕድሎችንና የገቢ ማግኛ መንገዶችን በቀጠናው መፍጠር እንደሚገባ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።
ዶ/ር ሙላቱ ይህን የተናገሩት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተዘጋጀ የፊልም ፌስቲቫል የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ነው።
የፊልም ኢንዱስትሪው በቀጠናው ተወዳዳሪ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዘርፉን ኩባንያዎች መገንባት እንደሚያስፈልግና እንደሚቻልም አንስተው ፥ የጋራ ዓላማችን የሆነውን የቀጠናችንን አንድነትና ብልፅግናን እስክናሳካ ይህን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል ዶክተር ሙላቱ።
ቀጣይ ፌስቲቫሎች ዕድሎችን ለማስፋትና በእጃችን ያሉን አቅሞች ለመረዳት ስለሚያግዙ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ፥ በፊልም ስራ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ዕጥረት መኖሩ፣ አገራዊ የፊልም ፖሊሲ አለመኖር ፣ ባለሙያዎችን የሚያሰለጥኑ አገራዊ ተቋማት ውስን መሆንና ከቅጂ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የፊልም ኢንዱስትሪው ዕድገት ተግዳሮቶች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ነው የገለጹት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተወሰኑ መሻሻሎች መኖራቸውንና በየዓመቱም በርካታ ፊልሞች መውጣት መጀመራቸውን በመልካም ጎን አንስተው ፥ ይህ መሻሻል የተገኘውም የኢትዮጵያ የፊልም ልማት ፖሊሲ በመጽደቁ ነው ብለዋል።
በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም መሰል ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹት ሚኒስትሩ ፥ በዘርፉ ካለው እምቅ ዕውቀትና ሃብት ለመጠቀም የቀጠናው አገራት በአንድነት መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የፊልም ፌስቲቫሉ የሥስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል መርሐ ግብር አካል ሆኖ እስከ ቀጣዩ እሁድ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቀጥል ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

