የአዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በቀጣይ ክረምት ለሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተከናወነ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ጎብኝተዋል።
በቀጣዩ ክረምት ለሚደረገው የ10 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዘጠኝ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች አራት ሚሊየን የተለያዩ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ኢንጂነር ታከለ ከዘጠኙ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ውስጥ በሁለቱ ጣቢያዎች በመገኘት እየተከናወነ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ በዛሬው ዕለት ተመልክተዋል።
የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎቹ አራት ሚሊየን ሀገር በቀል ዛፎችን በማፍላት ከባለፈው ክረምት የተሻለ አቅርቦትና ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ቀሪ ስድስት ሚሊየን የሚሆኑ የዛፍ ችግኞች ደግሞ በተቋማት የሚሸፈኑ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ኢንጂነር ታከለ በአዲስ አበባ ከባለፈው ክረምት የበለጠ ችግኞችን በተመረጡ ቦታዎች ለመትከል ከወዲሁ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት። እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከችግኝ ማፍላት ስራው በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ የቦታ ልየታ እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በጊዜ በማጠናቀቅ እንደ ከተማ የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ስራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ባሳለፍነው የክርምት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከሶስት ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

