አዲስ አበበ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል 804 ሺህ ሰዎች 3ኛውን ዙር የኮቪድ -19 መከላከያ ክትባት ወስደዋል፡፡
የክልሉ የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር አቶ አብዱፋራህ አህመድ እንደገለጹት÷ 3ኛው ዙር የኮሮና ክትባት ንቅናቄ በሶማሌ ክልል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ እስካሁን 804 ሺህ ወይም 54 ከመቶ ያህሉ ተከትበዋል፡፡
በክልሉ በሚገኙ 6 ከተማ አስተዳደሮች እና 93 ወረዳዎች በሚገኙ 17 ሆስፒታሎች 1 ሺህ 484 ጤና ኬላዎችና 212 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም÷ በተንቀሳቃሽ ቡድኖችና በዋና ዋና ከተሞች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎችና በትምህርት ቤቶች ነው ክትባቱ እየተሰጠ ያለው፡፡
3ኛው ዙር ክትባት ከመጀመሪውያና ሁለተኛ ዙሮች የተሻለ አፈፃፀም እንዳለው የገለፁት አቶ አብዱፋራህ አህመድ÷ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ በራስ ፍላጎት በመምጣት ክትባት እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ኮቪድ 19 የጤና እክል ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስስትል በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ12 አመት በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንዲወሰዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ክትባቱን የወሰዱ ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት÷ በራሳቸው ተነሳሽነት ክትባቱን እየወሰዱ መሆኑንና ባለፉት ዙሮች ምንም የጤና እክል እንዳላጋጠማቸው መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

