አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡሬ -ጎመር የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታን በተገቢው የጥራት ደረጃ እና በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የቡሬ – ጎመር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኝ እና አጠቃላይ ርዝመቱ 43 ኪሎ ሜትር ሲሆን÷ ለግንባታው የሚውለው አጠቃላይ የገንዘብ መጠንም 1 ቢሊየን 335 ሚሊየን ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡
አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የቅይጥ ግብርና እና የእንስሳት እርባታ የሚከናወንበት በመሆኑ መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው አርሶ አደርና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እደሚኖረውም ነው የተገለጸው፡፡
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ትከሻን ጨምሮ በከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር፣ በገጠር ደግሞ 10 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሰምረዲን አዳነ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት አጋማሽ መጀመሩን ገልጸው÷ እስካሁንም የአፈር ቆረጣ፣ ሙሌትና የስትራክቸር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማካሪ ድርጅቱ የፕሮጀክት ተጠሪ ኢንጅነር ዘገየ ጠና በበኩላቸው መንገዱን ከተያዘለት የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ጥራት የማንደራደርበት ጉዳይ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጥራት መስፈርት መሰረት እንዲጠናቀቅ ሥራችንን በተደራጀ ላብራቶሪ አስደግፈን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል መፍጠሩንና ሠራተኞቹ ከሥራ ዕድል ባለፈም ከፍተኛ የሆነ ሙያዊ ልምድ እየቀሰሙ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
መንገዱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር÷ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የአዝርዕት እና የፍራፍሬ ምርቶች ሳይበላሹ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲሁም በአካባቢው ወደሚገኙ ኢንዱስትሪ ዞኖች በጥራትና በፍጥነት ለማድረስ ያስችላል ተብሏል።
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

