Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ ሰርቲ በተባለ ስፍራ ማምሻውን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ።

የህዝብ ማመላለሻ ሚኒ ባስ መኪና ከተሳቢ ተሽከርካሪ  ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የደረሰው።

የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ፓሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ንጉሴ ሞገስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት እንደገለጹት አደጋው  የደረሰው ማምሻውን 12 ሰዓት ከ40 ላይ ነው።

በአደጋው በሚኒባሱ ከነበሩት  ሰዎች ውስጥ የስምንቱ ህይወት ወዲያው ማለፉንና አሽከርካሪውን ጨምሮ በ15 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው  ነው ብለዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ንጉሴ ሞገስ፥ የተሳቢው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

የህዝብ ማመላለሻ  ሚኒባሱ ወደ መቀሌ ተጓዦችን ይዞ ሲጓዝ እንደነበር ገልጸው የሟቾች ማንነትና አድራሻ  እየተጣራ ነው ብለዋል።

በግርማ ነሲቡ

Exit mobile version