Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኦሮሚያ ክልል ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
 
ድጋፉን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስረክበዋል፡፡
 
አቶ ሽመልስ በተፈጥሮ ሃብት የታደለው አዲሱ ክልል በልማት ተጠናክሮ ሃብቱን ጥቅም ላይ ያውል ዘንድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ጠላቶች በውስጥም በውጪም ሃገር ለማጥፋት ተግተው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ÷ ይህንን ማሸነፍ የሚቻለው ተባብሮ በመስራት ብቻ መሆኑን አመላክተዋል።
የሁለቱ ክልሎች ህዝብ የነበረውን ትስስር በማጠናከር ከሌሎች ክልሎች ጋር በጥንካሬ መራመድ ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ሽመልስ ።
 
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዛሬው ዕለት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ገብተዋል።
 
አቶ ሽመልስ ቦንጋ ሲደርሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የካፋ ዞን ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በቦንጋ ቆይታቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version