አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእኛ ዘመን ወጣት የአርበኝነት ሚና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ “የእኛ ዘመን ወጣት ሚና!” በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የተጽዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ÷ በሀገራችን ፈተና ሆኖ የቆየውን ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ፈተና የተሻገሩና ከሀብት ብክነት እና ከሌብነት የፀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ወጣቶቹ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም በአንድም በሌላም የተሳተፉበት ልማት ምን እንደሚመስል ለመገንዘብና በቀጣይም አሻራቸውን ለማሳረፍ ያነሳሳቸዋል ነው ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ የጠላት ሀገር የማፍረስ ፕሮጀክት ሳይሆን የአዲስ አበባ ብልፅግና ነው፤ የእኛ ዘመን ወጣት የአርበኝነት ሚና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ነው ብለዋል።
ሰላምና ልማት ለአፍታም የማይቆሙ የህልውናችን መሰረት ናቸው ያሉት አቶ መለስ÷ ወጣቶች ታሪካዊ ሚናቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን ሚና እንደማይለያቸው ማረጋገጣቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
“የእኛ ዘመን ወጣት ሚና!” በሚል የውይይት ሰነድ ያቀረበው የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ÷ ጠቅላይነት፣ ፅንፈኝነትና ተገንጣይነት፣ አፍርሶ መገንባት፣ ታታሪ ሰራተኛን ማወደስ ሲገባ በተለያየ መጠሪያ ማንኳሰስ እንዲሁም ስሜታዊነት አገራችንን ሲፈታተኗት እንደቆዩ አመላክቷል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

