Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግልገል በለስ- ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመንገድ ግንባታ ስራ ተጠናቆ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ከግልገል በለስ እስከ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚደርሠውን የመንገድ ግንባታ ስራ አጠናቆ አስመረቀ፡፡

ዋና መምሪያው 210 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን 3ኛ ደረጃ የጠጠር መንገድ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የጠጠር መንገድ በማሳደግ በተቀመጠለት የግዜ ሠሌዳ አጠናቆ ማስመረቁ ተገልጿል፡፡

የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ደስታ አብቼ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ በላቸው ካሳ መንገዱን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ሌተናል ጀኔራል ደስታ አብቼ ÷የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ የግልገል በለስ እስከ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመንገድ ፕሮጀክትን ስራ ሲረከብ የተሠጠው የመንገድ ፕሮጀክት ስራ ብቻ ሳይሆን ታላቅ አገራዊ ሃላፊነትና አደራም ጭምር ነበር ብለዋል።

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች ሲጓጓዙ በመንገድ ላይ እስከ ሁለት ሳምንት ይቆዩ እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡

አሁን ላይ የመሃንዲስ ክፍሉ ባከናወነው መንገድ የማሻሻል ጥገና ስራ የግድቡ የግንባታ ግብዓቶች በአንድ ቀን መድረስ ይችላሉ ብለዋል።

በምረቃ ስነ-ስረዓቱ ላይ የአካባቢው መስተዳደር አካላት፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

Exit mobile version