አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣2014(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን ውል ለተጨማሪ ስድስት ወራት አራዘመ፡፡
ውሉ ከመጋቢት 4/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ወራት እስከ መስከረም 2/2015 ዓ.ም ተራዝሟል፡፡
በመዲናዋ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ወደ ስራ ከገቡ በኋላ በየቀኑ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል ስምሪት እየተሰጣቸው የሚገኙ አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ቢሮው ውላቸውን መራዘሙን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ማህበራትም በውሉ መሰረት የተቀመጡ የአሰራር ስርዓቶችን ስራ ላይ በማዋል ከዚህ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ቢሮው አሳስቧል፡፡
በሁሉም አውቶቡሶች GPS በመግጠም የክትትልና ቁጥጥር ስራው የተጠናከረ እና አገልግሎት አሰጣጡም የተሻሻለ እንዲሆን በትኩረት እንዲከወንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ከጥቅምት 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶች በኪራይ መልክ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ የሚታወስ ነው።

