Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

7 የብረታ ብረት ንግድ ድርጅቶች ከ638 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እና ግብር መሰወራቸውን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰባት የብረታ ብረት ንግድ ድርጅቶች ከ638 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እና ግብር መሰወራቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባካሄደው ምርመራ እንደደረሰባቸው አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ አስቦና አገር የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥር መረቦችን ዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
ፖሊስ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ከተሞች ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ብረታ ብረትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማጣራቱን ከዚህ ቀደም ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ሰሞኑን ሰባት የብረታ ብረት ንግድ ድርጅቶች ከ638 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እና የንግድ ትርፍ ግብር መሰወራቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባካሄደው የወንጀል ምርመራ እንደደረሰባቸው አስታውቃል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ማንኛውም የንግድ ድርጅት ተጨማሪ እሴት ታክስ እና ግብር ስወራ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር የዕድገት ፀር የሆነ ህገ-ወጥ ድርጊት መሆኑን አውቆ የሚገባውን ታክስ እና ግብር በመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ታክስ እና ግብር በሚሰውሩና በሚያጭበረበሩ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ በተመሳሳይ መልኩ የወንጀል ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹንም ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version