አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መሪዎች ታሪካዊ ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን ከግምት በማስገባት በሦስት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
በፋይናንስ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ በጂቡቲ ጉብኝት አድርጓል፡፡
ልዑኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መልዕክት ለጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ባስረዳበት ወቅት÷ በጋራ ማንነት የተጋመደው የሁለቱ ሀገራት ሁሉ-አቀፍ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ መሆኑን አውስቷል፡፡
የሀገራቱን ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከግምት በማስገባትም መሪዎቹ ቀደም ብለው በተወያዩት መሰረት ሦስት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ተደርሷል።
በዚሁ መሰረት፡-
የአትክልትና ፍራፍሬ የዋጋ ተመንን በተመለከተ÷ የሁለቱ ሀገራት መንግስታት በሚያቋቁሙት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት የጂቡቲን አሁናዊ ገበያ እና የሰፊውን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ የዋጋ ማሻሻያ እስከሚደረግ ድረስ ለጂቡቲ ብቻ ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ተወስኗል።
ለ40 ዓመታት ሲሠራበት የቆየው ወደ ጂቡቲ የሚላከው የጫት ምርት ታሪፍ ከፍ ለማድረግ ቀደም ብለው መሪዎቹ በተስማሙት መሰረት ተግባራዊ እንደሚደረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የጂቡቲ አስመጪዎች የጫት ምርት የውጭ ሽያጭ ውል ምዝገባ መፈፀም ሳይጠበቅባቸው÷ ምርቱን ማስገባት እንዲችሉ እንዲሁም የባሕር አገልግሎት ክፍያዎች በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት የሚመለከታችው አካላት በጋራ ምክክር ተደርጎበት ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ማስተካከያው ሳይደረግ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል።
በተጨማሪም ልዑኩ÷ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የንግድ እና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ መሐመድ ዋርሳማ ዲሬህ፣ የንግድ ም/ቤት ሊቀ መንበር አቶ ዩሱፍ ሙሳ ደዋሌህ እንዲሁም የጂቡቲ ወደቦች እና ነጻ የንግድ ቀጠና ባለስልጣን ሊቀ መንበር አቶ አቡበከር ዑመር ሐዲን አግኝቶ በሀገራቱ መካከል ስላለው የዲፕሎማሲ፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ወደብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡
እንዲሁም ልዑኩ በጂቡቲ በነበረው ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የተጣራና ድፍድፍ የምግብ ዘይት ምርት አቅራቢ ድርጅት ጎልደን አፍሪካን መጎብኘቱና ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር መወያየቱ ተመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!