Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህብረተሰቡ ሰላሙን በማጠናከር በመተከል ዞን የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ከግብ ማድረስ እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ከግብ ለማድረስ ህብረተሰቡ የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተገለጸ።

የቤኒሻንጉል ክልልና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚያተኩሩ ጉዳዮች ዙሪያ ከግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዞኑ እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር ተከትሎ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ እጩ ዶክተር አቢዮት አልቦሮ ገልጸዋል።

የዜጎችን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ፥ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ በየደረጃው ካለው አመራር ጋር በቅርበት መስራት እንዳለበት አብራርተዋል።

በከተሞች አካባቢ እየተስተዋለ ያለውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስወገድ አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተሰጠውን ሃላፊነት እንዲወጣ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ የተናገሩት ደግሞ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ናቸው።

የግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ኑራ ሳልህ በበኩላቸው ፥ በከተማዋ ያለውን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመፍታት ነዋሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ የመሳተፍና ነጻ ሃሳብ የማንጸባረቅ ልምዳቸውን ማዳበር እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎች እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በተገኘው ሰላም መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ ቢሆንም በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ስርቆትና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የሚመለከተው አካል በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በግልገል በለስ ከተማ እየተስተዋለ ያለውን የስርቆት ወንጀል ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለውን የጸጥታ ሃይል በመቀናጀት ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version