Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሽል አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሽል አሳሰበ፡፡
 
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ የኮሚሽኑን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡
 
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ÷ ኮሚሽኑ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 80 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ መድረሱን ገልጸው÷ የፊዚካል እና የበጀት አፈጻጸሙም ተመጣጣኝ መሆኑን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡
 
አፈጻጸሙ የተሻለ ነው የተባለው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ከዕቅዱ አንጻር ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ÷ ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ከምትፈልገው የአገልግሎት አሰጣጥ እና ከዜጎች እርካታ አንፃር ከኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
 
ኮሚሽኑ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚነሱ ቅሬታዎችን በ“ጊዜ የለኝም!” እሳቤ መፍታት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
 
በቀጣይም ኮሚሽኑ በትኩረት አቅጣጫ ያስቀመጣቸውን ነጥቦች መተግበር እና ለውጡንም ከራሱ ከኮሚሽኑ ከአመራር እና ከባለሙያው መጀመር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
 
የዘርፉ ለውጥም ሀገራዊ እንዲሆን ከፌዴራል እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት፡፡
 
ሲቪል ሰርቪሱ የተሻለ እና ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በማሰማራት ላይ በትጋት እንዲሠራ እና ይህንን አቋሙን በግልጽ ማሳወቅ እንዳለበት ማሳሰባቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የኮሚሽኑ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም የተሻለ እንዲሆን ቋሚ ኮሚቴው በተጠናከረ አያያዝ ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርግ እና አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው በሚሄዱበት ጊዜ የተቻላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
 
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶከተር መኩሪያ ኃይሌ በበኩላቸው÷ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ለቀጣይ ሥራዎቻቸው በግብዓትነት እንደሚጠቀሙበት ነው የተናገሩት፡፡
Exit mobile version