አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያውያንን አብሮነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ የጥላቻ ንግግሮችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግስት ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አሳሰቡ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጥላቻ ንግግሮችን በሚያስተላልፉ አካላት እና መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፣ ከትግራይ ዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ (ትዴትፓ) እና ከሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ፓርቲ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፥ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር በወጣው ህግ መሰረት መሰል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግገሮችን እና ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ሊጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲ ትብብር ፓርቲ (ትዴትፓ) ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፥ ዋልታረገጥ የሆነ አመለካከት እውነታውን ካለመገንዘብ የሚመነጭ ስህተት መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ የጥላቻ ንግግሮች የማህበረሰቡን የእርስ በርስ መስተጋብር ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት ልዩነትን የማስፋት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም አውስተዋል።
ስለሆነም መሰል የጥላቻ ንግግሮች እና ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት በተገቢው ሁኔታ ተለይተው በህግ ሊጠየቁ ይገባል ነው ያሉት።
በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችን የመቆጣጠሩ ሂደት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ሊቀ መንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ፥ በየትኛውም ሁኔታ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎች ህዝብን ለማጋጨት ያለሙ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መሰል መልዕክቶች የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር ባህል እና የህዝቡን አንድነት ብሎም ግንኙነት የሚሸረሽሩ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አመራሮቹ የህዝቡን አንድነት ሊያጠናክሩ በሚገቡ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሃይለኢየሱስ መኮንን

