Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ርስቱ ይርዳ እና አቶ አህመድ ሽዴ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ችግኝ ተከሉ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ እና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የ4ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካል በሆነው በከምባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ችግኝ ተክለዋል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ለማሳካት በተካሄደው ችግኝ ተከላ ላይ፥ የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አንዲሁም የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳ በችግኝ ተከላው ላይ፥ በክልሉ ባለፉት 3 ዓመታት ከ3 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።

ዘንድሮም ከ1 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው÷ “ሀገራችን የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለማሳካት በከምባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ከሕዝባችን ጋር ችግኝ ተክለናል” ብለዋል።

“ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ወደ ሕዝቡ ወርደን መስራታችን ሕዝቡ ለስራው እንዲነሳሳ ከማድረጉም ባሻገር ፍቅርና መዋደድን ያጠናክራል” ነው ያሉት።

ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በኋላ÷ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ አዋዬ ቀበሌና ሺንሺቾ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባትና የማደስ ስራ አስጀምረዋል።

በዚሁ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር÷ ሁላችንም በያለንበት ለወገኖቻችን መድረስ ይጠበቅብናል፤ ስንደጋገፍ አብረን እናድጋለን፤ አቅም አንሷቸው በችግር ላሉ ወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ እንደገለጹት÷ በክረምት የዜግነት አገልግሎት ስራዎች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባትና የማደስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በቢቂላ ቱፋ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version