አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በታንዛኒያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚጀመር አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት በብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ እና በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ መሪነት የተመራው የኢትዮጵያ ጳጳሳት ልዑካን ቡድን በ20ኛውን የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ታንዛኒያ ዳሬሰላም አቅንቷል፡፡
ልዑካኑ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው በታንዛኒያ የኢፌዴሪ ልዩ መልክተኛና ባለሙሉስልጣን ከአምባሳደር ሽብሩ ማሞ ጋር ተወያይተዋል።
ለልዑካን ቡድኑ በታንዛኒያ በስደት በእስር በአስከፊ ሁኔታላይ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰፊው ማብራሪያ የተደረገላቸው ሲሆን÷ በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያም ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ሽብሩ በታንዛኒያ 5 ሺህ የሚደርሱ ህጻናት እና ወጣት ወንዶች በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪ ደላሎች ተታለው አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የታንዛኒያን ድንበር ጥሰው በመግባታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በእስር ቤቱ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል የተወሰኑት ለዓመታት ተፈርዶባቸው የታሰሩ ሲሆኑ÷በአብዛኛው ግን የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ገንዘብ ስለሌላቸው በታንዛኒያመንግስት ትብብር በእስር ቤቱ የሚቆዩ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢምባሲ በታንዛኒያ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትእና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር የእሥር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶችን ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት መቃወስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ስደት የሚያስከትለውን ሞት እና አስከፊ ገጽታ እጅግ አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
በታንዛኒያ የሚደረገው የጳጳሳት ጉባኤ የአካባቢ ጥበቃ መቃወስ በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቀነስ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስደት ሁለንተናዊ እድገትን ከማሳጣት አልፎ ለሃገራትም ትልቅ ፈተና በመሆኑ የሐይማኖት ተቋማት እና የመንግስት አካላት በመተባበር የወጣቶችን ህይወት መታደግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በአሁኑ ወቅት በእስር ቤት የሚገኙትወጣቶች የመሰረታዊ ፍላጎቶች የምግብ፣ የመጠጥ እና የንጽህና መጠበቂያ እቃዎች በተቻለ ፍጥነት በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና በጎ ፍቃድ ያላቸው ሁሉ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

