Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት 100 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር በጀት አጽድቋል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በለውጡ ሂደት የተቀመጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጥራት ያለው ኢኮኖሚ እንዲኖር ማረጋገጥ፣ ምርትና ተወዳደሪነትን በማሳደግ ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በጥራት ማቅረብ፣ ተቋማዊ ለውጥን ማረጋገጥ፣ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ መሪነት ማረጋገጥ፣ የሴቶችና ወጣቶችን ፍትሃዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የከተማ ውበት ስራዎችን ማጠናከር በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸው ተገልጿል።

በጀቱ ከ2014 በጀት ዓመት በ41 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱም ነው የተጠቆመው፡፡

ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ ግቦችን ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት (ለውሃ፣ መንገድ፣ ለፈጠራ ስራ) እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ በመደልደል ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ትኩረት መደረጉም ነው የተጠቀሰው፡፡

አስተዳደሩ የተያዘውን በጀት ለልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማዋል ቢያቅድም÷ ሁሉንም የከተማውን ሕዝብ የልማት ጥያቄና ፍላጎት በዚህ በጀት ብቻ መፍታት እንደማይቻል በመገንዘብ ነዋሪዎች ለአካባቢ የልማትና የፀጥታ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቅስ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ርብርብ እንዲያደርጉም ተጠይቋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version