አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ምንም አይነት የነዳጅ እጥረት እንደሌለ እና የዋጋ ጭማሪ አለማድረጉን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አመራሮች እና የክፍለ ከተሞች ንግድ ፅህፈት ቤት ሃላፊዎች ሰሞኑን እየታየ ያለውን የነዳጅ ፍላጎት እጥረት በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደገለጹት፥ ባለፉት ቀናት በከተማዋ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል በሚል በአንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች የመኪና ሰልፍ መብዛት ተስተውሏል፡፡
በአንጻሩ በከተማዋ ምንም አይነት የነዳጅ እጥረትም ሆነ የዋጋ ጭማሪ አለመደረጉን ነው ሃላፊው የተናገሩት።
ችግሩ በአንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች የወሩ መጨረሻ አካባቢ የዋጋ ለውጥ ይመጣል በሚል ነዳጁን ለመያዝ ባደረጉት ህገ ወጥ ስራ ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ቢሮው ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በከተማዋ ባሉት ነዳጅ ማደያዎች ቢሮው የቁጥጥር ስርዓቱን አጠናክሮ በመቀጠል በአጭር ቀናት ውስጥ ችግሩን ለማስተካከል በትኩረት እንደሚሰራ ሃላፊው መናገራቸውን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

