Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ክልል በበጀት አመቱ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 በጀት ዓመት በደቡብ ክልል ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ገለጹ፡፡

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ሲሆን÷ ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ አቅርበዋል።

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች 504 ሺህ 894 ስራ አጥ ዜጎች ተለይተው በቋሚና በጊዜያዊ ለ306 ሺህ 51 ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀዋል።

ለተደራጁ ስራ አጥ ዜጎች መነሻ የሚሆን እና በፍጥነት ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ከ929 ሺህ ብር  በላይ እንደተሰራጨም ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 21 ሺህ 333 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን እና ከ126 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና መሰጠቱንም ነው የገለፁት።

በስራ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች 544 ሚሊየን 445 ሺህ ብር በበጀት ዓመቱ እንዲቆጥቡ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ በኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ውዝፍ ሆኖ ያለውን 1 ቢሊየን 113 ሚሊየን 107 ሺህ ብር ለማስመለስ ታቅዶ 772 ሚሊየን 281 ሺህ ብር ማስመለስ መቻሉንም ገልፀዋል።

ለኢንተርፕራይዞች፣ ለጥቃቅንና አነስተኛና ማህበራት ማምረቻና መሸጫ ቦታ የሚሆን 5 ሺህ 222 ሄክታር መሬት መተላለፉንም አቶ ርስቱ ይርዳ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ግብርናን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት÷ በ2013/2014 በጀት ዓመት መኸር እርሻ በአዝዕርት እንዲሁም በአበባና አትክልት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር በመሸፈን ከ99 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን አመላክተዋል፡፡

በበጋ የስንዴ ምርት 6 ሺህ ሔክታር በስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ 5 ሺህ 109 ሄክታር መሬት መሸፈን መቻሉን ጠቁመው÷ ከዚህም 152 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል።

ከወጪ ምርት እና ከቁም እንስሳት ግብይት 48 ሚሊየን 262 ሺህ 953 ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

በቢቂላ ቱፋ

Exit mobile version