Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ለሰላም መስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር ዓለሙ ስሜ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ለአካባቢው ሰላም መስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ አሳሰቡ።

ዶክተር ዓለሙ ስሜ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወከሉበት የአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት ዶክተር ዓለሙ ባደረጉት ንግግር፥ በአሁኑ ዘመን በአስተሳሰብ የበላይነት ካልሆነ በስተቀር በአፈሙዝ ትግል የሚመጣ ነፃነት የለም ብለዋል።

ወያኔ ከቤተ መንግስት ተሸንፎ የወጣው በአፈሙዝ ሳይሆን ወጣቱና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ጨምሮ የለውጥ ኃይሎች ባደረጉት የአስተሳሰብ አንድነት ትግል መሆኑን አውስተዋል።

አሁን አሸባሪው ሸኔ እያደረገ ያለው ከ50 ዓመት በፊት የነበረና ምንም ውጤት ሳያስገኝ ግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ ከንቱ ሂደት ነው፤ ትግሉ እውነት መስሎዋቸው ወደ ጫካ አብረዋቸው የገቡ የኦሮሞ ልጆችን ያስጨረሰ ነበር ብለዋል ዶክተር ዓለሙ።

የአሁኑ ትውልድና ሕዝቡ የአሸባሪው ሸኔን የተላላኪነት ሚና በሚገባ መገንዘብ እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ለአካባቢው ሰላም መስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር ዓለሙ ስሜ፥ የአርሲ አርባጉጉ በተለይም የመርቲ ወረዳ ሕዝብ አንድነቱን ጠብቆ ለሰላም እየከፈለ ላለው ትግል ማመስገናቸውንም የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

አሁንም አንዳንድ ወጣቶች ተታልለው የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው የሽፍታ የጥፋት ተልዕኮ ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንዳይሆኑ ሕዝቡ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ለአሸባሪው ሸኔ የዘጋውን በር መክፈት እንደሌለበትም ነው የጠቆሙት።

መንግስት በአሸባሪው ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃና የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ተግባሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ ማስቀጠሉንም ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version