Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን በስምንት ወረዳዎች ከ11 ሺህ በላይ ሄክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይ የተከሰተውን የሰብል አውዳሚ ተምች ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በምንጃር ሸንኮራ፣ በረኸት፣ ሀገረ ማርያም፣ አንጎለላና ጠራን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች ስር በሚገኙ 57 ቀበሌዎች ተምች ተከስቷል፡፡

በዞኑ በ56 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተደረገው አሰሳ በተያዘው ሐምሌ ወር 11ሺህ 300 ሄክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት በሰብል አውዳሚ ተምች መወረሩን ገልጸዋል፡፡

ሰብል አውዳሚ ተምቹ የተከሰተው አነስተኛ የዝናብ መጠን ባለባቸው አካባቢዎች በተፈጠረ የአፈር ሙቀት ምክንያት መሆኑን ገልጸው የዝናቡ መጠን በጨመረ ቁጥር አውዳሚ ተምቹ እየጠፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡፡

አውዳሚ ተምቹን ለመከላከል ከኮምቦልቻ የዕፅዋት ህክምና ማዕከል እና ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘውን 3 ሺህ ሊትር ጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከአርሶ አደሩና ከግብርናው ዘርፍ ተዋንያን ጋር በመተባበር ተምቹ ከተከሰተበት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን 2 ሺህ 500 ሄክታር በሰብል የተሸፈነ መሬት ከተምች ነፃ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

በሰሜን ሸዋ ዞን የፀረ ተባይ መርጫ መሳሪያ የሌለው አርሶ አደር የለም የሚሉት የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ፥ በማሳ ላይ አሰሳ በማድረግ ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ከተከሰተ በኋላም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም አካላት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

Exit mobile version