አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ሰርጎ ለመግባት የሞከረውን አልሸባብ በመደምሰስ ተቆርጠው የቀሩ የሽብር ቡድኑን አባላት የማጽዳት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የሀገር መከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ተናገሩ።
ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ እንደገለጹት፥ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልና በምዕራብ ኢትዮጵያ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ተከትሎ ሰላም የሰፈነ ሲመስላቸው ሰሞኑን በምስራቅ ኢትዮጵያ የማጥቃት ሙከራ አድርገዋል።
የአልሽባብ አሸባሪ ቡድን በሶማሌ ክልል በአምስት ትናንሽ የጠረፍ አካባቢዎች ማለትም በየድ፣ አቶ፣ ኤልብርዴ፣ ዋቃሾና ፈርፈር አካባቢዎች ለማጥቃት ቢሞክርም በጸጥታ ኃይሉ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልና አመራርም የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ የነበረው ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የአልሽባብ ታጣቂዎች በአንድ አካባቢ ብቻ ሰርገው ገብተው የነበረ ቢሆንም፥ የጸጥታ ኃይሉ ከበባ በማድረግ ከ100 በላይ የሽብር ቡድኑን አባላት ደምስሷል ነው ያሉት።
ቡድኑ ለሽብር ዓላማው ሲጠቀምባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተቆርጠው የቀሩ የሽብር ቡድኑን አባለት የማጽዳት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሽብር ቡድኑ ላይ በተወሰደው እርምጃ፥ መትርየስ አር ፒ ጂ እና ሌሎች ከባድ የቡድን መሳሪያዎች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ከቡድኑ አባላት ተማርከዋል።
በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የሀገሩን ዳር ድንበር እያስከበረ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ፥ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለክልሉ ልዩ ኃይል ከፍተኛ የሞራልና የስንቅ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ሙሉ በሙሉ በቀጣናው መግባቱንም ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመድፈር የሚሞክሩ ኃይሎች ላይ ሙሉ እርምጃ ለመውሰድ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!