አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደሮች እና ልዩ መልዕክተኞች ወደ መቀሌ እንዲጓዙ መፈቀዱን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳስታወቁት፥ እርሳቸው እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ በፌደራል መንግስት አቋም ዙሪያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ህብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኞች እንደዚሁም ለዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ጉዳይ ፈፃሚ፣ ለፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመንና ብሪታኒያ አምባሳደሮች ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም ገለፃ ወቅት የሰላም ውይይትን በተመለከተ የፌደራል መንግስት አቋምን ግልፅ ማድረጋቸውን ነው ያመላከቱት።
በዚህም መሰረት፥ የፌደራል መንግስት የሰላም ውይይቱን በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን እንደዚሁም የሰላም ውይይቱ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መጀመር እንዳለበት ግልፅ ተደርጓል ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ውይይት ሂደት በሌሎች ወገኖች የሎጀስቲክ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚችልም ነው የተገለፀላቸው።
ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን ምቹ የትብብር አውድ ለመፍጠር እና ከኮሚሽኑ ጋር ያለን ልዩነት ለማጥበት የፌደራል መንግስቱ እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በዚሁ ገለፃ ላይ አምባሳደሮቹ እና ልዩ መልዕክተኞቹ ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ እንደሚችሉ ፈቃድ እንደተሰጣቸውም ይፋ እንደተደረገ አምባሳደር ሬድዋን ጠቁመዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

