አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በባለፈው በጀት ዓመት የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ አስታወቁ፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱን የስራ ሂደት ግምገማ በማጠናቀቅ የ2015 በጀት ዓመት የስራ እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።
በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ለሁለት ቀን የተካሄደውን ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ የመሩት ሚኒስትሩ የ2014 ዓ.ም የስራ ሪፖርት ካደመጡ በኃላ እንደተናገሩት ፥ ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው በጀት ዓመት የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር።
እንደ ተቋም ከፍተኛ የሀገር ሃብትን የሚያስወጡ የምርት ግብዓቶችን ከመግዛት ይልቅ አምራች ስራ ላይ በመሳተፍ ወጪን የመቀነስ ስራ መስራት ለበለጠ ግዳጅ ብቁ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
የ2015 በጀት ዓመት እቅድ በ2014 በጀት ዓመት የነበሩ እጥረቶችን የሚሞላ ስራ መስራት ይገባል ማለታቸውን ከመከላያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአዲሡ በጀት ዓመት ቀዳሚ የሆነውን የዝግጁነት ስራ ከመስራት ጎን ለጎንም ተቋማዊ ኢንዱስትሪዎችን የማጠናከር፣ በራስ አቅም ማምረት እና የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ አማራጮችን በመውሰድ ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ተቋማት ትርፋማነታቸውን የሚያሰፉ ሰራዎችን አጠናክሮ በመስራት የሰራዊቱንና የቤተሰቡን ኑሮ የሚያቀሉ፣ መከላከያ ፋውንዴሽን የጀመራቸው በሁርሶ እና በብላቴ ማሠልጠኛ ማዕከል የሚሰሩ የግብርና ስራዎችን በሌሎችም በማስፋት በምግብ ምርቶች እራስን የመቻል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ጀኔራሎች እና ከፍተኛ መኮንኖች ከባለፈው የበጀት ዓመት የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር በ2015 በጀት ዓመት ውጤታማ ስራ ለመስራት ውይይቱ አስተማሪ እንደነበር ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!