አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ካለው ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አንጻር ችግሩን በመንግስት ብቻ ለመፍታት ስለሚያዳግት የግሉ ተቋማት ከመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።
አሠሪና ሠራተኛን የሚያገናኘው ሁለተኛው የሥራ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽንና ባዛር ተከፍቷል፡፡
አውደ ርዕዩን መላ ኤቨንት ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት አዘጋጅተውታል፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አውደ ርዕዩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት ÷ ዜጎች አምራች ሆነው የሀገር ተስፋ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ይህ ዓውደ ርዕይ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ካለው ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አንጻር ችግሩን በመንግስት ብቻ ለመፍታት ስለሚያዳግት የግሉ ተቋማት ከመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አንስተዋል ፡፡
በዓውደ ርዕዩ ላይ ከ50 በላይ ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ህጋዊ እውቅና ያላቸው ኤጀንሲዎች የተሳተፉ ሲሆን አውደ ርዕዩ አነስተኛና መካከለኛ ትምህርትና ክህሎት ያላቸው ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በመጀመሪያው ዙር አውደ ርዕይ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን በዚህኛው ዙር ካለፈው አመት የላቀ ቁጥር ላላቸው ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እንደታቀደ ተገልጿል ።
ለሁለት ቀን የሚቆየውን አውደርዕይ ከ15 ሺህ በላይ ስራ ፈላጊዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

