Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቻይናው ፕሬዚዳንት “በታይዋን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል” ሲሉ ጆ ባይደንን አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳን ሺ ጂንፒንግ በታይዋን የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል ሲሉ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን አስጠነቀቁ፡፡

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ታይዋን ለማቅናት እቅድ መያዛቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይድን በታይዋን ጉዳይ ዙሪያ ለሁለት ሰዓት የዘለቀ የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም ፕሬዚዳንት ሺ አሜሪካ የቤጂንግን “የአንድ ቻይና መርህ” ማክበር እንዳለባት ነው በጥብቅ ያሳሰቡት፡፡

የታይዋን ነፃ አገር የመመስረት ሂደት የማይታሰብ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ÷በጉዳዩ ላይ የውጭ ኃይሎች የሚያሳዩትን ጣልቃ ገብነት ኮንነዋል፡፡

በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ጆ ባደን በታይዋን የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያሳዩት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ”በእሳት እንደመጫዎት ይቆጠራል፤ በእሳት የሚጫወትም መቃጠሉ አይቀርም” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው፥ አሜሪካ የታይዋንን የነፃነት ጥያቄ የሚገዳደር እና አሁን ያለውን ሰላም እና መረጋጋት ለማደፍረስ በአንድ ወገን የሚወሰድን የተናጠል እርምጃ አጥብቃ እንደምትቃወም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ዋሽንግተን በታይዋን ጉዳይ ላይ ያላት አቋም እና ፖሊስ አሁንም ያልተለወጠ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሌላ በኩል ፔሎሲ በእቅዳቸው መሰረት ለስራ ጉብኝት ወደ ታይዋን የሚጓዙ ከሆነ ቻይና ጠንካራ አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹን አልጀዚራ ዘግቧል።

ዩናይትድ ስቴትስ በታይዋን የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት መሰል ግጭት-ቀስቃሽ ድርጊቶች ከመፈጸም እንድትቆጠብም አሳስቧል፡፡

ቻይና ታይዋንን እንደ አንድ የተገነጠለች የራሷ ግዛት አድርጋ የምታያት ሲሆን÷ ታይዋን ግን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ነው የምትቆጥረው።

Exit mobile version