Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሰሜን ኮሪያ ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመመከት ዝግጁ ነኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸው ከየትኛውም አካል ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት በኒውክሌር የጦር መሳሪያ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

ፒዮንግያንግ በፈረንጆቹ 1950 እስከ 1953 የተካሄደውን የሁለቱን ኮሪያዎች ጦርነት ያስቆመውን የጦር ሠራዊት 69ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በትናንትናው ዕለት አክብራለች፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን÷ ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ላይ ራስን የማጥፋት መርህን በመከተል ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዋሽንግተን እና ሴኡል የኒውክሌር ሚሳኤሎችን በደቡብ ኮሪያ ለማከማቸት እቅድ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአንፃሩ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካም ሆነ ከየትኛውም አካል ሊቃጣ የሚችልን ወታደራዊ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ለመመከት ዝግጁ መሆኗን ነው የገለፁት::

ለዚህም ሰሜን ኮሪያ ስታበለጽግ የቆየችውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አገልግሎት ላይ ለማዋል አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች ነው ያሉት፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳሏት የሚገመት ሲሆን÷ በዓመት ተጨማሪ ስድስት እና ሰባት ሚሳኤሎችን ማምረት እንደምትችልም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኪም ቤተሰብ አባላት ከዓለም አቀፍ ማዕቀብ እፎይታ ለማግኘት በማሰብ ምዕራባውያንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣትና ልማትን ለማሳደግ ወይም የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲዝቱ ቆይተዋል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን ትንኮሳ ተከትሎ የሰሜን ኮሪያ ጦር የሚያደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version