አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር ተወያዩ።
አቶ ደመቀ ለልዩ መልዕክተኛው መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ገልጸውላቸዋል ።
በአፍሪካ ህብረት መሪነት በናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ተጀራሽነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉም ለልዩ መልዕክተኛው አስረድተዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ሙሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ወቅት የህወሓት ቡድን በተቃራኒው እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይገባልም ነው ያሉት።
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች አድንቀዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ አበረታች መሆኑን በውይይታቸው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

