አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርና ሠራተኞች በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተለያዩ አካባቢዎች ችግኝ ተክለዋል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የአመራርና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በዛሬው ዕለት ከ2 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን በደብረ ብርሃን ከተማ በሬሳ ወንዝ አካባቢ ተክለዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አመራርና ሠራተኞች 4ኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በማስመልከት በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት አካባቢ ችግኝ ተክለዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ እንደገለጹት÷ በዛሬው መርሐ ግብር 10 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው ቀጣይም ችግኞችን መትከልና መንከባከባችን ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ችግኝ ተክለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው÷ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ አየር መንገዱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡
አየር መንገዱ 100 ሺህ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ የያዘ ሲሆን ዛሬ ያካሄደው መርሐ ግብር የመጀመሪያው ዙር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በእታገኝ መኮንን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

