Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምስራቅ ሸዋ ዞን ለወንጀል ድርጊቶች ማስፈፀሚያ ሲውሉ የነበሩ 377 ሞተር ሳይክሎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን 7 ወረዳዎች በተካሔደ ድንገተኛ ፍተሻ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ማስፈፀሚያ ሲውሉ የነበሩ 377 ሞተር ሳይክሎች መያዙን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለጹት፥ የተያዙት ህገ ወጥ ሞተር ሳይክሎች የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው፣ ቦሎና የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ያልለጠፉ ናቸው ።

ሞተር ሳይክሎቹ የትራፊክ ህግ ጥሰው በመንቀሳቀሳቸውና በተለያዩ የወንጀል ተግባር ውስጥ በመሳተፍ መጠርጠራቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ከተፈቀደው የጭነት መጠን በላይ መንገደኞችን በመጫን ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተመላክቷል።

ለአብነትም በቅርቡ በአንድ ሞተር ሳይክል አምስት ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ ታዝሎ የነበረ ህፃን ከእናቱ ጀርባ አምልጦ በመውደቁ በጅብ መበላቱን አስታውሰዋል።

በሞተር ሳይክሎቹ ዝርፊያና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የመሳሰሉ ተግባራት ይፈፀማል ያሉት ኮማንደር አስቻለው፥ በረብሻ ወቅት ቤንዚን በማመላለስ የግልና የመንግስት ንብረት እንዲቃጠል በማድረግ መጠርጠራቸውም ተጠቁሟል።

እርምጃው በህገ ወጥ ሞተር ሳይክል በመታገዝ የሚፈፀሙ ስርቆቶችንና የተለያዩ ወንጀሎችን ከምንጩ ለማድረቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በቀጣይም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version